“ወጣቱ ዲሞክራሲን የመገንባት ኃላፊነት አለበት”
መኢአድ
ሚያዝያ 27 ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመታት የጣሊያን ወረራ ነጻ የወጣችበትንና አርበኞች በድል ወደ አዲስ አበባ የገቡበትን 68ኛውን የድልና የነጻነት በዓል በአራት ኪሎ የድል ሐውልት አርበኞችና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን በተገኙበት የመላው የኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ምክትል ፕሬዝዳንትና የምስራቅ ኢትዮጵያ ቀጣና ኃላፊ ሻለቃ ጌታቸው መንግስቴ የድል በዓሉን በተመለከተ ለአንድነት ጋዜጣ እንደገለፁት የኢትዮጵያ ሕዝብ የአርበኝነት ተጋድሎውን በላቀ መንፈስ የገለጠበትና አንድነቱን ያሳየበት ነው ብለዋል፡፡ ሕዝቡ ለነጻነቱ ሲል በጣሊያን ወራሪ ኃይል ፕሮፖጋንዳና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ሳይበገር ጾታና እድሜ ሳይለይ በአርበኝነት የታገለበትና ድል የተቀናጀበት ዕለት መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ሚያዝያ 27 የድል በዓል ሲከበር እስካሁን በሕይወት ለመቆየት የቻሉት ጥቂት አባትና እናት አርበኞች ከነ ትጥቃቸው በወኔ የነበረውን ትግል እንዴት እነደነበር ሲገልፁ ማየት ለአዲሱ ኢትዮጵያዊ ትውልድ የሚያኮራ ነው ያሉት ሻለቃ ጌታቸው መንግስቴ የአሁኑ ትውልድ ከነዚህ ቀደምት አርበኞች የነጻነት ዋጋንና የሐገር ፍቅርን ብዙ ሊማሩት የሚገባ ቁም ነገር አለ በማለት አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው ታሪኩን ያሳለፈው ከውጭ ከመጡ ወራሪ ኃይሎችና ከራሱ አምባገነን መሪዎች ጋር እልህ አስጨራሽ በሆነ ትግል ሲሆን ለዲሞክራሲ ልዕልና የሚያደርገው አሁንም ትግል ዛሬም መፍትሄ አላገኘም፡፡ በመሆኑም ዛሬ ከወራሪ የውጭ ጠላት ነጻ የሆንበትን የድል በዓል ሲያከብር ለዲሞክራሲ ልዕልናና ለመልካም አስተዳደር መመስረት ዛሬም እየታገለ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ስለሆነም ከዛሬ 68 ዓመት በፊት ጀግኖች አርበኞች የፋሺስት ወራሪ ኃይልን ድል ያደረጉበትን ቀን ስናከብር የአሁኑ ትውልድን በሰላማዊ መንገድ በመታገል ነጻና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን እንደሚገነባ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
መኢአድ እየተከተለ ባለው የሰላማዊ የትግል ስልት የፓርቲው አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች የሕይወት፣ የአካልና የንብረት መስዋእትነትን መክፈላቸውን ጠቁመው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነትና መብት ተከብሮ እስኪረጋገጥ ድረስ መኢአድ ከሕዝቡ ጋር በሰላማዊ መንገድ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሻለቃ ጌታቸው አብራርተዋል፡፡
አርበኝነት ጠብመንጃ በመያዝ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ውጤታማ የሆነ ሁሉ የሐገሪቱ ጀግና መሆኑን የገለፁት ሻለቃ ጌታቸው ወጣቱ ትውልድ ሐገሩን በልማት በመገንባትና በሰላማዊ መንገድ በመታገል ነጻነቱን የማስከበር ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
የመኢአድ ምክትል ፕሬዘዳንት እንዳሉት የድል በዓሉን ስናከብር በአያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አዕምሮ የሚታወሰው አገራችን በኢኰኖሚ ራሷን ችላ ለዜጐቿ የተመተቸና በታሪኳ ብቻ ሳይሆን በዕድገት የሚመኩባት አገር ለመሆን የሚያስችላትን ስርአትና አስተዳደር ለመመስረት ዛሬም በእልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ እንደምትገኝ ተገንዝቦ ለትግሉ ሁሉም የዜግነቱን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አብራርተዋል፡፡
ጠላትን በተባበረ ክንዱ ድል ማድረግ ልማዱ የሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም በድህነትና በኋላቀርነት ላይ የጋራ ክንዱን ማንሳት እንዳለበት ገልፀው የዓለምን የዴሞክራሲ ስርዓት ለራሳቸው ጥቅም በሚመች መልኩ አዛብተው የሚተረጉሙትን አካላት በሰላማዊ መንገድ ሊቃወሟቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የድልና የነጻነት በዓል ለአምስት ዓመታት በዱር በገደል ሲዋጉ የነበሩት የኢትዮጵያ አርበኞች በብዙ መስዋእትነት የራሳቸውንና የሐገራቸውን ነጻነት አስከብረው አዲስ አበባ የገቡበት የመታሰቢያ ቀን ነው፡፡