የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ በመላው የሐገሪቱ ክፍሎች 63 ጽ/ቤቶችን መክፈቱን የፓርቲው ሕዝብ ግንኙት ኮሚቴ ኃላፊ ወ/ሪት መሶበወርቅ ቅጣው ለአንድነት ጋዜጣ ገለፁ፡፡
ከቅንጅት አመራሮች መፈታት በኋላ የተወሰኑ የአመራር አባላት እራሳቸውን ከቅንጅት ፓርቲ ቢያገሉም በኢንጂነር ኃይሉ ሻውል የሚመራው ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ከአባላትና ደጋፊዎች ጋር በመሆን ፓርቲውን የማጠናከር ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ኃላፊዋ ጠቅሰዋል፡፡
ቅንጅት ጠቅላላ ጉባኤውን ሰኔ 2 2000 ዓ.ም ካካሄደና ስያሜውንም ነሐሴ 2 2000 ዓ.ም ወደ መኢአድ ከቀየረ በኋላ ፓርቲው ይበልጥ ተጠናክሮ በሰሜን ፣ በምስራቅ በምእራብና በደቡብ ኢትዮጵያ ቀጣናዎች 28 የዞንና 35 የወረዳ ጽ/ቤቶች እንደተከፈተ ተገልፀዋል፡፡
የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ በሀገሪቱ ባሉ ክልሎች የፓርቲውን የጽ/ቤቶች ብዛትን በመተንተን ሲያስረዱም በደቡብ ኢትዮጵያ 32፣ በሰሜን ኢትዮጵያ 20፣ በምስራቅ ኢትዮጵያ 5፣ በምእራብ ኢትዮጵያ 4፣ የዞንና የወረዳ ጽ/ቤቶች እንዲሁም በአዲስ አበባ 2 ጽ/ቤቶች እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡
አብዛኛዎቹ የወረዳ ጽ/ቤቶች ሕዝቡ ለፓርቲው ካለው ፍቅርና ድጋፍ እንዲሁም ለሰላማዊ ትግል ባለው ቀናና ቁርጠኛ አመለካከት ፓርቲው ከሚያደርገው ድጋፍ ውጭ አባላት በራሳቸው ተነሳሽነት በግላቸው የጽ/ቤቶችን ኪራይና ሌሎች ወጪዎችን በመሸፈን የፓርቲውን ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የሐገሪቱ ክፍሎች ፓርቲው ጽ/ቤቶችን እንዲከፍት ጥሪ እያደረጉ የሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች ብዙ ናቸው ያሉት ወ/ሪት መሶበወርቅ መኢአድ ወደፊት ጥያቄ ባቀረቡ ዞኖችና ወረዳዎች ላይ ጥናት በማድረግ ጽ/ቤቶችን ለመክፈት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡
የቅንጅት አመራር አባላት እስር ቤት ሲወጡ በመላው ሀገሪቱ የነበሩት ጽ/ቤቶች በገዥው ፓርቲ ተዘግተው የነበረ ሲሆን የቀሩትም ከአምስት የማይበልጡ እንደነበሩና መኢአድ ግን ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ የጽ/ቤቶቹን ቁጥሮች ወደ 63 ማሳደግ መቻሉ ፓርቲው በሕዝብ ዘንድ ያለውን ድጋፍና ተቀባይነት በግልጽ የሚያሳይ ነው ሲሉ የሕዝብ ግንኙት ኃላፊዋ ወ/ሪት መሶበወርቅ ቅጣው ገልፀዋል፡፡