መኢአድ “ሊበራል ኦፕን-ኤየር ኮሌጅ” መክፈቱን አስታወቀ
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ለአንድ ዓመት ያህል በጽ/ቤቱ ግቢ ውስጥ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት “ሊበራል ኦፕን-ኤየር” በሚል ወደ ኮሌጅ ደረጃ ማሳደጉን የመኢአድ ምክትል ፕሬዝዳንትና የምእራብ ኢትዮጵያ ቀጠና ኃላፊ አቶ አሰፋ ኃብተወልድ ለአንድነት ጋዜጣ ገለፁ፡፡
በተጨማሪም የሊበራል ዲሞክራሲ ከሌሎች የዲሞክራሲ ዓይነቶች ጋር ያለውን ልዩነት በማነጻፀር ግንዛቤ ለመስጠት የተጀመረው የትምህርት መርሐ ግብር ከጥቅምት 3ዐ ቀን 2ዐዐ1 ዓ.ም ጀምሮ በኮሌጅ ደረጃ መስፋፋቱን አስታውቀዋል፡፡
በአለፈው አንድ አመት ውስጥ በፍልስፍና፣ በርእዮተ ዓለም፣ በፖለቲካ፣ በሳይንሳዊ ነክ ጉዳዮች፣ በሰብአዊ መብቶች፣ በሕግ ጽንሰ ሐሳብና በሌሎችም ርእሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትምህርት መስጠቱንም አብራርተዋል፡፡
የኮሌጁ ስያሜ እንደሚያመለክተው መማር ለሚፈልጉ ሁሉ ለፓርቲ አባላትም ሆነ ለሌሎች ክፍት መሆኑንና የትምህርት ቦርዱም ከፍተኛ የትምህርት ዕውቀት ባላቸው አባላት እንደሚመራ ጠቁመው ቦርዱ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የሥራ እቅድ ማውጣቱን አቶ አሰፋ አስረድተዋል፡፡
የመኢአድ ም/ፕሬዝዳንት ስለ ኮሌጁ ዓላማ ሲገልፁ ኮሌጁ የፓርቲውን ትግል ስልት መሰረት በማድረግ አባላትንም ሆነ ሌሎችን በሊበራል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ፍልስፍናና መርህ ለማነጽ እና መንግስትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችና ግለሰቦች በእውቀትና በሰላማዊ ስርአት እንዲታገሉ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኮሌጁ የሚሰጠው ትምህርት የፓርቲው አባላትም ሆኑ ደጋፊዎች እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ፖለቲካዊና ማሕበራዊ ችግሮች ላይ ሳይንሳዊ የሆነ ግንዛቤና የጠራ አቋም እንዲኖራቸው ብሎም ችግሮችን ለመፍታት በንቃትና በቆራጥነት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ትምህርቱን የሚሰጡ መምህራን በጋራ ወይም በተናጠል እንደሚያስተምሩና በማመር ማስተማሩ ሂደት ወቅት የመድረክ መሪና አወያይ እንደሚኖር አቶ አሰፋ ገልፀው ለወደፊት ኮሌጁ የመኢአድ መደበኛ ኮሌጅ እስኪሆን ድረስ ጥረቱ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
በጥቂት አባላትና በክፍል ውስጥ ይሰጥ የነበረው ትምህርት እያደገ መጥቶ ዛሬ በፓርቲው ጽ.ቤት ውስጥ በሚገኘው ህዝባው ድንኳን ውስጥ በአማካኝ 300 ተሳታፊዎች የሚገኙበትና ፕሮግራሙም ሳያቋረጥ ዘወትር እሁድ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ የሚካሄድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ኮሌጁ በተማሪዎችና በበጐ አድራጊዎች ድጋፍ የራሱ የሆነ የገቢ አቅም እንዳለውና ለትምህርት አገልግሎት የሚውሉ ቁሳቁሶችን እያሟላ መሆኑንና ወደፊትም የገንዘብ አቅሙን ለማሳደግ ጥረት እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡