መንግስት ጐንደር ውስጥ ከ6ዐ በላይ ሰዎችን ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ለአርባ ቀን ያሕል አስሮ መልቀቁ ተገለፀ፡፡
የ2001 ዓ.ም የጥምቀት በዓል መከበርን ተከትሎ የገዥው ፓርቲ በኦርቶዶክስና በእስልምና ሐይማኖቶች መካከል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ተጠያቂ በማድረግ 6ዐ በላይ ሰዎች ያለፍረድ ቤት ትእዛዝ ለአርባ ቀናት ያህል አስሯቸው እንደነበር ተገለፀ፡፡
አቶ ያሬድ ግርማ የመኢአድ ማዕከላዊ ምክር ቤት አባልና የሰሜን ጐንደር ሰብሳቢ በዞኑ ውስጥ ባላቸው ከፍተኛ ተደማጭነት ምክንያት ከሥልሳዎቹ ጋር በተመሳሳይ ውንጅላ ታስረው እንደነበረ አቶ ጌታነህ ዓለም የመኢአድ ላዕላይ ምክር ቤት አባልና የሰሜን ኢትዮጵያ ቀጠና አደራጅ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ጌታነህ ገለጻ ታሳሪዎቹ በሃይማኖት ሰበብ ይያዙ እንጂ በዚህ አጋጣሚም የተቃዋሚ ፓርቲ አባለባትም እንዲታሰሩ ተደርገዋል፤ ለምሳሌ አቶ ያሬድ ግርማ በግጭቱ ወቅት በቦታው ያልነበሩና በሰላም ወዳድነታቸውም በአከባቢው የታወቁ እንደነበሩ አስታውቀው መንግስት ጠንካራ የመኢአድ አባል በመሆናቸው ብቻ እረብሻውን አሳቦ አብሮ በማሰር አርባ ቀን እንዳጉላላቸው ጠቅሰዋል፡፡
ይህ የመንግስት እርምጃ ፍጹም የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደሆነ ከሚያሳዩ ነገሮች መካከል፡-
- ይህን ያህል ሰው የታሰረው ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጭ ህገወጥ በሆነ መንገድ መሆኑ፣ ታሳሪዎቹ ድርጊቱ በተፈፀመበት የጥምቀት ቦታ አለመኖራቸውና ከየቤታቸው መለቀማቸው፣ ለአርባ ቀናት ሲታሰሩ ምንም ዓይነት መረጃና ክስ ሳይቀርብባቸው መሆኑና ወንጀል እንዳልፈፀሙ እየታወቀ አቃቤ ሕግ ጉዳዩ ከዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በላይ ነው በማለት ወደ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይዛወር ብሎ ለፍርድ ቤቱ ሐሳብ ማቅረቡና ካለ ሶስት ሺ ብር ዋስ አትለቀቁም በማለት ሰላማዊዎቹን ሰዎች ማስጨነቅ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
ይህ የሚያሳየው በአሁኑ ወቅት ያለው የሕግ አሰፈፃሚ አካል አሠራር ለኢህአዴግ እና ለኢህአዴጋውያን ብቻ እንጂ ለሌሎች ዜጐች ያልቆመ መሆኑን ያረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡